በማእከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት፣ በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ቤተክህነት፣ ከጎርጎራ ከተማ 5 ኪሎሜትር …. በቅዱሳን ገዳማት እንደ ከዋክብት በታጠረው በታላቁ ጣና ሐይቅ ዳርቻ… በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንዱና ቀዳሚው መንፈሳዊ ማዕከል ይገኛል። በ1326 ዓ/ም የተመሠረተዉ ማን እንደ አባ አቡነ ያሳይ መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም፡፡ ይህ የወንዶች ገዳም በቀድሞ የቦታው ስም “መድበይ”፤ በኋላም “ደብር ቅዱስ” ተብሎ ይጠራ ነበር።
“ማን እንደ አባ” የሚለው ስም ከገዳሙ መሥራች፣ ከጻድቁ አባታችን አቡነ ያሳይ ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው። ጻድቁ አቡነ ያሳይ ከንጉሥ ዘር የተገኙ ሲሆኑሲሆኑ፣ አባታቸውም የኢትዮጵያ ንጉሥ ቀዳማዊ ዓምደ ጽዮን ናቸው። የአልጋ ወራሽነት ማዕረግን ተቀብለው ክብረ መንግሥትን ይጠባበቁ ነበር። ነገር ግን፣ ወደ ቤተ-መንግሥቱ ከሚመጡ መነኮሳት ጋር ሲወያዩ እና “ሰው ዓለሙን ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢጎዳ ምን ይጠቅመዋል?” የሚለውን መለኮታዊ ቃል ሲያሰላስሉ፣ ያን የንጉሥ ልጅነት ክብርን እና የንግሥና ዙፋኑን ናቁት። ዓለምን ትተው ወደ አክሱም ደብረ በንኮል ገዳም በመሄድ፣ ከሌሎች ስድስት ወንድሞቻቸው ጋር፣ ከታላቁ አባት ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኩስናን ተቀበሉ። እኒህም ሰባቱ ከዋከብት የሚባሉት ቅዱሳን አባቶች፡ አቡነ ያሳይ ዘማን እንደ አባ፥ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፥ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየጻ፥ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬዛ፥ አቡነ አብሳዲ ዘዞዝአንባ፥ አቡነ ያፈቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ፥ አቡነ ዮሐንስ ዘግራናቄ፡ ናቸው፡፡
ጻድቁ ከደብረ በንኮል ወደ ጣና ሐይቅ የመጡት ከመንፈስ ወንድሞቻቸዉ ከአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና ከአቡነ ያፈቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ ጋር ሲሆን፣ ከአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጋር በቀድሞ ስሙ መደባይ ተብሎ በሚጠራው ቦታ አብረዉ ተቀመጡ። አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፡ በዚች ቦታ ስምንት ክንድ ጥልቀት ባለው ጉድጓድ (ዋሻ) ውስጥ ዐሥራ ሁለት ዓመታት ከተጋደሉ በኋላ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾላቸው፡ “ይህች ቦታ የወንድምህ የያሳይ ናት፤ የአንተ መካነ ገድል ግን ዋሊ (ዋልድባ) ነው” ብሏቸዋል።
የአቡነ ያሳይ ትልቁ ተአምርና የገዳሙ ስያሜ ምንጭ የሆነው ታሪክ እዚህ ይጀምራል። ጻድቁ አቡነ ያሳይ፡ ከደቡብ የሀገራችን ክፍል ሐዋርያዊ አገልግሎታቸዉን ፈጽመዉ ወደ ገዳማቸው ሲመለሱ ልብሳቸውን (አፅፋቸውን) በጣና ሐይቅ ላይ አንጥፈው ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ያሻግራሉ። እርሳቸው ደግሞ፣ ታቦተ መድኃኔዓለምን ይዘዉ፣ ዛሬም በገዳሙ በክብር የምትገኘውን ይህችን ድንጋይ እንደ ታንኳ ተጠቅመው ሐይቁን ተሻገሩ፥ እስከ ዕለተ እረፍታቸዉ ድረስ ሲጠቀሙባት ነበር።
ይህን ተአምር ያዩ ሰዎችም “የሚሰጥመውን ድንጋይ በባሕር ላይ የሚያንሳፍፍ ማን እንደ አባ ያሳይ!” ብለው በመገረም ጮኹ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፡ ይህ ስም የቅዱሱ ቦታ መጠሪያ ሆነ።
በአጽፋቸዉ የተሻገሩት ደቀ መዛሙርት አቡነ ቶማስ ዘብርጊዳ፣ አቡነ እንድርያስ ዘአንጋራ፥ አቡነ ዘካርያስ ዘገሊላ እና አቡነ ክርስቶስ ብርሃን ዘቀንዶ ናቸዉ።
ገዳሙ አባቶች በጋራ የሚኖሩበት፣ በጋራ የሚጸልዩበት፣ በጋራ የሚሠሩበት የአንድነት ገዳም ነው። አሁን የምናየው ይህ ታሪካዊ ቤተ መቅደስ፣ ጻድቁ አባታችን ካነጹት በኋላ በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት የታደሰ ነው። ሕንጻ ቤተክርስቲያኑም ቅዱሳን ሐዋርያትን የሚወክሉ 12 ዐበይት ዓምዶች አሉት።